ንዳድ ፡ ትኩሳቱ የማይቻለው የወባ ህመም
- Zebeaman Tibebu
- Apr 7
- 3 min read
Updated: Apr 8
ትኩሳት፡ ትኩሱ የትምህርት ተስፋ
የዛሬ አምስት አመት በፊት የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ ፤ ወደ ዩንቨርስቲ የተመደበው ጉጉው ተማሪ፤ ቀጣዩ ህይወትን የሚያቀናበትን የእውቀት ስንቅ ለመሰነቅ ፤ ትምህርቱን እና ነገውን ብቻ አስቦ ፤ ነበር ጥቅምት ላይ የተጓዘው። በወቅቱ ግን ስለወባ ህመም አደገኝነት ሆነ ፤ ስለወባ መከላከያ መድሀኒት መውሰድ ፤ ብዙም እውቀት አልነበረውም ነበር።

በፊት በመሀል አዲስ አበባ ይኖር የነበረ ይህ ተማሪ ሀሳቡ ጭንቁ መሀል የወባ በሽታ አልነበረም። የሚማርበት ዩንቨርስቲ ያለበት አከባቢ ወባ የተንሰራፋበት ስለነበር ፤ ትምህርቱን በጀመረ ገና በሁለተኛ ወር ላይ ፤ ትኩሳት፣ ራስ ምታት እና ብርድብርድ የሚል ስሜት ይሰማው ጀመር። ግቢው ውስጥ ሌሎች ተማሪዎች ሲታመሙ ቢያይም ፤ ፈተና ወቅት ላይ ስለታመመ ፤ ህመሙ ሲጠንከር ነበር ወደ ህክምና የሄደው። ባደረገው ምርመራ ፋልሲፓረም እና ቫይባክስ የሚባሉ የወባ ተህዋሳት ደሙ ላይ ስለታየ ወዲያውኑ ህክምና ጀመረ።
መድሀኒቶቹን በጀመረ በቀናት ጊዜ ውስጥ ምልክቶች መጥፋት ጀመሩ። ከህመሙ በሙሉ ቢያገግምም ፤ በህመም ላይ ሆኖ የተፈተነው ፈትና ውጤት ተበላሸበት። በዩንቨርስቲ ቆይታው ሙሉ ድንገት እረፍት ካጣ ወይም ምግብ ከተራበ ፤ የወባ ህመሙ (ቫይቫክስ) እያገረሽ ያስቸግረው ነበር።
ይህ ወባ ወደተንሰራፋበት አከባቢ ለትምህርት ወይም ለስራ የሚሄዱ ሰዎች ታሪክ ነው። ይህ ተማሪ በህክምና እርዳታ ቢተርፍም ፤ ብዙ ኢትዮጵያውያን በየአመቱ በወባ ይሞታሉ።
የወባ/ንዳድ በሽታ ከጥንት ጀምሮ የኢትዮጵያ ህዝብን (በተለይም በቆላው አከባቢ የሚኖሩ ማህበረሰቦች) ሲያጠቃ የኖረ ህመም ነው። የሐረር አገረ ገዢ የነበሩት ፤ የአጼ ሚኒሊክ ቀኝ እጅ የ አጼ ኃይለስላሴ አባት ራስ መኮንንም ሳይታሰብ የሞቱት ፤ በዚሁ በንዳድ በሽታ ነው።
📍 የወባ ጫና በኢትዮጵያ ፡ ሀገር አቀፍ አደጋ
ወባ (በተለምዶ ንዳድ) የሚባለው ህመም ፤ በ ወባ ትንኝ አማካኝነት የሚያጋጥም ህመም ነው። በኢትዮጵያ በተለይም ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህጻናት እና ነፍሰ ጡር እናቶችን ከሚያጠቁ እና ለሞት ከሚዳርጉ ዋነኛ ህመሞች አንዱ ነው።

እ.ኤ.አ በ 2024 የዓለም ጤና ድርጅት እንደገለጸው፡-
እ.ኤ.አ. በ 2024ዓ.ም በመጀምሪያ 10 ወራት ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ 7.3 ሚሊዮን የወባ በሽተኞች ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ፤ ከ እነኝህም ማዕከል ከ 1157 የሚሆኑት በወባ ምክንያት ሞተዋል።
ከኢትዮጵያ ህዝብ ውስጥ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው ፤ የወባ በሽታ በተጠቁ ወይንም በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች ይኖራሉ።
በአብዛኛው የአገሪትዋ ክፍል ወባ በዋነኝነት የሚንሰራፋው ፤ ክረምትን ተከትሎ ባሉት የመጀመሪያ ወራት (መስከረም እስከ ታህሣሥ) ነው። ይህም የወባ አስተላላፊ የሆነችው ትንኝ መራባት ጋር ይያያዛል።
ዋነኛው ወንጀለኞች

የወባ በሽታን የሚያመጡ አምስት የበሽታ አምጪ ተሕዋሳት ቢኖሩም በዋነኝነት በኢትዮጵያ የሚጠቀሱት ሁለት አይነቶች ናቸው። እነኝህም፦
ፕላዝሞዲየም ፋልሲፓረም፡ በሽታው የጠነከረ ፣ ፈጣን ፣ ጥቃቱ የደረጀ ፣ ገዳይ እና ለብዙ ወባ ሞት ተጠያቂ ነው።
ፕላዝሞዲየም ቫይቫክስ፡ በመድሀኒት ቢታከምም ፤ ጉበት ውስጥ ተደብቆ ፤ ሰውነት ሲደክም ፤ እያገረሽ ለረዥም ጊዜ የወባ ህመም የሚያመጣ ተሕዋስ ነው።
🚨ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?

ወባ ወዳለበት አከባቢ ከተጓዙ እና በድንገት እነኝህን ምልክቶች ካሳዩ ፤ አይቆዩ በአፋጣኝ ወደ ህክምና ተቋም ሄደው ምርመራ ያድርጉ።
ህመሙ ሲጀምር ቀለል ባለ ድካም፣ ራስ ምታት ፣ ብርድ ብርድ ማለት እና ትኩሳት ሊኖረው ይችላል። እንደ ጉንፋን የሚመስል ምልክትን አንዳንዴ ስለሚያሳይ ፤ የወባ ህመምን የማያቅ ታማሚን እንዲዘናጋ ያደርገዋል።
ዋና ዋና ምልክቶቹ መሀል የሚከተሉት ይገኙበታል።
ከፍተኛ ትኩሳት (እያረፈ የሚመጣ ወይም ፣ ማቋረጥ የሌለው ሊሆን ይችላል)
ትኩሳቱን ተከትሎ ላብ ይኖራል
ብርድ ብርድ ማለት እና ማንቀጥቀጥ
ራስ ምታት (ከባድ የሆነ)
ድካም
የጡንቻ እና የመገጣጠሚያ ህመም
ማቅለሽለሽ እና ማስታወክ
የሆድ ህመም
የምግብ ፍላጎት ማጣት
እጅጉን ከጠነከረ፡
ጭንቅላት ላይ በሚኖረው ተጽእኖ ነገሮችን አለማስተዋል(ኮንፊዩዝድ) እንዲሁም ኮማ
ኩላሊት ላይ ጥቃት አድርሶ የኩላሊት ህመም
የቀይ የደምሴል ቁጥር መመነምን
የአተነፋፈስ ሁኔታ ላይም ችግር ማጋጠም
እጅጉን ከገፋ ደግሞ እስከሞት ሊያደርስ ይችላል።
💡 ምልክቶቹ ወዲያውኑ በትንኟ እንደተነደፍን አይታዩም ፤ ይልቁኑ የበሽታ አምጪ ተህዋሱ ደምውስጥ ገብቶ እስኪራባ ከ10-15 ቀናት ይቆያሉ ።
🎯 የኢትዮጵያ ራዕይ፡ ወባን ማጥፋት

በአለም ዙሪያ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በወባ በሽታ በየአመቱ እየሞቱ በመሆኑ ፤ የተባበሩት መንግስታት እየሞቱ በመሆኑ ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ለአለም ሀገራት ያወጣው የዘላቂ ልማት ግብ ውስጥ አካቶታል (Sustainable Development Goals)።
ግቡም በውስጡእ.ኤ.አ በ2030 የወባ እና ችላ የተባሉ የትሮፒካል ወረርሽኖችን ማቆም ያካትታል።
የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴርም በበኩሉ ከአለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመተባበር የወባ በሽታን በቀጣይ አምስት አመት ውስጥ ፈጽሞ ለማስወገድ ፤ የወባ መከላከል እቅድ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል።
እየሰራባቸው ያሉት ዋነኛ ጉዳዮች ፦
የቅድመ ምርመራ እና ፈጣን ሕክምናን ማጠናከር
ኬሚካል የተነከረ አጎበር ስርጭትን እና የቤት ለቤት የወባ መድሀኒት ርጭትን(IRS) ማስፋፋት
በማህበረሰብ ውስጥ የወባ ክትትልን ማጠናከር፣ ዲጂታል ሪፖርት ማድረግ
የወባ ትንኝ ማራቢያ ስፍራዎችን/ማቆሪያዎችን ማጥፋት
💉 አዲሱ ተስፋ፡ መከላከያ መድሀኒት እና ክትባት

ማንኛውም ሰው መውሰድ የሚችላቸው የመከላከል መጠናቸው ከሳምንታት እስከወራት የሆኑ ፤ ወባን የሚከላከሉ የመድሀኒት አማራጮች (ኬሞፕሮፋይላክሲስ) አሉ። ይህ ደግሞ እንዲሰጥ የሚመከረው፦
ወባ ወደተንሰራፋባት ስፍራ ለሚጓዙ ተጓዦች እና
ወባ ህመም በተንሰራፋበት አከባቢ ለሚኖሩ እርጉዝ ሴቶች ነው።
አሁን አለም በደረሰበት የህክምና ደረጃ ወባ በተንሰራፋበት አከባቢ ለሚኖሩ ህጻናት የወባ ክትባት (Mosquirix) ተሰርቷል።
ኢትዮጵያ ላይ እስከ አሁን መጠቀም ባንጀምርም ፤ አቅርቦትን ለመፍጠር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።
በተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ያለው መረጃ ክትባቱ ተስፋ ሰጪ ውጤት አስመዝግቧል።
🧍🏾♂️በግለሰብ ደረጃስ ምን ማድረግ ይችላሉ?
ወባን ለመዋጋት የግድ የጤና ባለሙያ መሆን አያስፈልግም። በበኩልዎ የሚከተሉትን በማድረግ ስርጭቱን መቀነስ ይችላሉ፡-
🛏️ በኪሜካል በተነከረ አጎበር አልጋዎትን ይከልሉ። በወባ አከባቢ የሚኖሩ ከሆነ ከአመት አመት ያድርጉ።
🏡 የወባ ትንኝ መራቢያዎችን ከመኖሪያ አከባቢዎ ያጥፉ። ማንኛውም ዉሀ ማቆር ከሚችል ስፍራን ( ጎማዎች ፣ ድስት ፣ ጉድጓድ ፣ ወ.ዘ.ተ...) ውሀ ያጥፉ ።
🏃🏽♂️ ምልክቶቹን ካዩ ሳይውሉ ሳያድሩ በፍጥነት እርምጃ ይውሰዱ። በአቅራቢያዎ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ይሂዱ።
📣የራስዎንም ሆነ በዙሪያው ያሉ ሰዎችን የወባ ህመም ግንዛቤ ያሳድጉ። ስለወባ ስርጭት እና መከላከያ መንገዶች ይወቁ ፤ ለሌላም ያጋሩ።
💬 ይህ ትግል የኛ ነው!
Comments