የተሰረቀ ልጅነት፡ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በኢትዮጵያ
- Zebeaman Tibebu
- 4 days ago
- 4 min read
ይህንን በሚያነቡበት ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ አንድ ህጻን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተጠቃ ይገኛል። በልቶ ሳይጠግብ ፤ ወደ ትምህርት ቤት የሚጓዝም ልጅ አለ። በድህነት የሚያስፈልጋትን መመገብ የተሳናት ፤ ጸንሳ የተራበች ፤ አንድ እናት አለች። ልጇን በደንብ ለመመገብ ፤ የጡት ወተት ትታ ፤ በቆሮቆሮ ወተት እያሳደገች ያለች እናት አለች።

የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሁልጊዜ ከረሀብ ጋር አይገናኝም። መልኩ —አቅማቸው የደከሙ ፣ ጉጉ የህጻናት አይኖች ብቻ ሊሆን ይችላል። መልኩ የተሳለ አእምሮ መጥፋት ፣ በትምህርት መውደቅ ሊሆን ይችላል። አናስተውለውም እንጂ ፤ የአንድ ልጅ የነገ አቅሙ በዛሬ ምግብ እጥረት እየተመዘበረ ነው። ይህ አስከፊ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በየእለቱ በፀጥታ እየተከሰተ ይገኛል።
ከበስተጀርባ ያሉት ቁጥሮች
ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ በህጻናት ጤና ላይ ጉልህ መሻሻል አሳይታለች። ሆኖም ግን ፤ አሁንም ያለው ቁጥር እጅጉን አሳሳቢ ነው። በቅርብ የወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ፡-
በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከአምስት አመት በታች ከሆኑ ህጻናት መካከል አንድ ሶስተኛ በላይ የሚሆኑት (38.6%) ተቀንጭረዋል — ለእድሜያቸው በጣም አጭር ናቸው።
ሰባት ፐርሰንት የሚሆኑት ደግሞ አሳሳቢ የሰውነት ክሳት አለባቸው—ለቁመታቸው በጣም ቀጭን ናቸው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 20 ህጻናት ሶስቱ በከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት (SAM) ይጠቃሉ።
ይህ ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በአለም ደረጃ ከ 5 አመት በታች ላሉ ህጻናት ሞት ዋነኛ ተጠያቂ ነው።
ካስተዋልን
ከእያንዳንዱ ቁጥር ጀርባ ቢያንስ አንድ ህጻን አለ። ወደፊት መሐንዲስ፣ ዶክተር፣ ኢንጂነር፣ ፓይለት የመሆን ተስፋ ያለው ፤ አንድ ጨቅላ ህጻን አለ። ይህ ህጻን ራሱን ሳያቅ ነገው እየተሰረቀ ነው። የተስፋው ሌባዎች ደግሞ የአመጋገብ ጉድለት እና የዘገየ እርምጃ ናቸው።
መቀንጨር ምንድን ነው? ስለመቀንጨር ማወቅ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

መቀንጨር የ ቁመት ማጠር አይደለም። ቁመት በተፈጥሮም ይሁን ወይም በተለያየ ህመም ምክንያት ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል። መቀንጨር ሥር የሰደደ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ጋር ተያይዞ ፤ የሰውነታችን የቁመት መጠን በተፈጥሮ መሆን ከሚችልበት ሳይደርስ በቋሚነት ሲገታ ነው። ይህም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምልክት ነው።
በተለይም በመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ውስጥ (ከልጁ መፀነስ ጀምሮ እስከ ህጻኑ ሁለተኛ አመት ድረስ) ያለው የአመጋገብ ሁኔታ ፤ የአንድን ህጻን እድገት እንዲሁም ቁመና ይወስናል። በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰውነቱ በመገንባት ላይ ይገኛል። የነርቭ ህዋሳት ተፈጥረው ስለሚያልቁ ፤ የአእምሮ አቅም ይወሰናል። የበሽታ መከላከያ ስርአት አወቃቀርም ፈር የሚይዘው በዚህ ጊዜ ውስጥ ነው። ለዚህም በዚህ ጊዜ ውስጥ የተመጣጠነ ምግብ በበቂ ሁኔታ የተመገበ ልጅ ፤ በትምህርቱ ውጤታማ፣ የአስተሳሰብ ምህዳሩ የሰፋ ፣ የበሽታ የመከላከል አቅሙ የደረጀ እንዲሁም አድጎ በስራው ውጤታማ ይሆናል።
በበቂ ደረጃ የተመጣጠነ ምግብ ያልተመገቡ ልጆች በበኩላቸው ፤ ከቁመናቸው ባሻገር ህይወታቸውም የተቀነጨረ ይሆናል።
ሩጫ ውድድር ላይ ነዎት እንበል፤ እርሶ ውድድሩን ከመነሻው እንዳይጀምሩ ተከልክለው ወደ ኋላ ብዙ ርቀት ተመልሰው እንዲጀምሩ ቢገደዱስ? ከዚህም አልፎ የሚሮጡት ያለ ጫማ ቢሆንስ?
እንደ አበበ በቂላ አሸንፋለው እንደማይሉ እርግጠኛ ነኝ። የማሸነፍ እድሎት አይርቅም? ውድድር ውስጥ ከሌላው እኩል ለመሆን አታካች አይሆንቦትም?
በተመጣጠነ ምግብ ጉድለት ቋሚ ለውጥ የመጣባቸውም ህጻናት ፤ አቅማቸው በምግብ ጉድለት ከተፈጥሮአዊ ደረጃው ተሰርቋል። ለዚህም መሆን የሚችሉት ፣ መስራት የሚችሉት ፣ ማትረፍ የሚችሉት የተፈጥሮ አቅማቸው ላይ አይሆንም።
ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት፡ አስጊው ችግር
ከመቀንጨር አንጻር ይህ ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እጅጉን አስጊ ችግር ነው። መቀንጨር ቋሚ ለውጥ ከማምጣት ፤ የተፈጥሮ አቅምን በቋሚነት ከማሳነስ ባሻገር ፤ አፋጣኝ የህክምና እርዳታ የሚያስፈልገው ችግር አያስከትልም። በተቃራኒው ከባድ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸው ህጻናት ፤ ያለው የምግብ እጥረት ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ፤ ሰውነታቸው ስራውን በስርአት እንዳይሰራ እክል ያጋጥመዋል። ከጸጉራቸው እና ከቆዳቸው ጀምሮ እሰከውስጥ ሰውነት አካላት ስራቸው ይስተጓጎላል።

እነኝህ ህጻናት ሰውነታቸው የውሀ እጥረት ይኖርበታል። ሲታዩ የከሱ ፣ እንደ ህጻን ልጅ ድንቡሽቡሽ ሳይሆን ጉንጫቸው የጎደጎደ፣ የደረት አጥንታቸው የወጣ፣ ሆዳቸው ያበጠ ፣ ጸጉራቸው መልኩ ለውጦ መቅላት የጀመረ፣ እንዲሁም እግሮቻቸው ያባበጡ ሊሆኑ ይችላሉ። የሰውነታቸው የበሽታ መከላከል አቅም ስለተመናመነም ፤ ደግመው ደጋግመው በበሽታ ይጠቃሉ።
ይህንሙሉ በሙሉ ልንከላከለው የምንችለው ሰቆቃ ነው። በህክምና እርዳታ የከፋ ችግር ሳያስከተል ወይም ሞት ሳያደርስ መመለስ ይቻላል።
ነገር ግን በዚህ የተነሳ በሺዎች የሚቆጠሩ ፤ የአገራችን ተስፋ የሆኑ ፤ ቦርቀው ያልጠገቡ ህጻናት በየዓመቱ ይሞታሉ።
ይህ ለምን ይከሰታል?
ሀገራችን ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባት ፤ በምሮቶቿ ህዝቦቿን መሉ በሙሉ መመገብ አቅም ያልደረሰች መሆኗ አለምአቀፋዊ እውነታ ነው። ባለፉ አመታት ይህንን ለማሻሻል ጥረት ብታደርግም ፤ ይህ የምግብ እጥረት በበርካታ ምክንያቶች እየተባባሰ ይገኛል። ለዚህም የ አየር ንብረት ለውጥ ፣ ድርቅ እና የግጭቶች መባባስ ተጠቃሽ ናቸው። የንፁህ ውሀ አቅርቦት እና የንጽህና አጠባበቅ ውስንነትም ለዚህ ተጠያቂ መንስኤ ይሆናሉ።
ከዚህ ባሻገር ትልቅ ድርሻ የሚወስደው የእናቶች አመጋገብ ልምድ ነው። የነፍሰጡር እናቶች አመጋገብ የተገደበ ከሆነ ፤ በ ማህፀን ውስጥ የጽንስ እድገት ይገደባል። ይህም የአመጋገብ ችግር ደግሞ ፤ በእናቶች የግንዛቤ ጉድለት እና የ ኢኮኖሚ አቅም ሊመጣ ይችላል። ከወሊድ በኋላም እናቶች የጡት ማጥባት እና የተጨማሪ ምግብ አሰጣጥም ይህንን ችግር ሊያባብሰው ይችላል።

አንዱ ጋር መስበር ካልተቻለ ፤ ይህ የምግብ ጉድለት የማይለቀን ተወራራሽ አዙሪት ነው። በድህነት/ በእውቀት ማነስ ምክንያት የተመጣጠነ ምግብ ጉድለት የነበረባት እናት ፤ አርግዛ ክብደቱ ያነሰ ህጻን ትወልዳለች። ልጇ የተመጣጠነ ምግብ ሳትበላ ታድጋለች። በዚህም መቀንጨር ያጋጠማት ልጅም ጎልምሳ ስታረግዝ ፤ በተቀነጨረ ማህጸኗ ውስጥ የሚያድገው ጽንስም እድገቱ ይገደባል። ይህ ዑደት ይቀጥላል። ስለዚህ ለእናቶች ግንዛቤ ሰጥተን ፤ አቅማቸውን ገንብተን ፤ የተመጣጠነ ምግብ አቅርበን ፤ ይህንን አዙሪት ማቆም ይኖርብናል።
የተሰወረው ዳፋ፡ የከሸፈው የኢኮኖሚ ኃይል
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ተጽእኖ ከጤና ተሻግሮ ፤ አገራዊ ምርታማነትን እና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ያሰናክላል። ገና በለጋ እድሜያቸው በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የተጎዱ ወጣቶች ትምህርታቸውን የማቋረጥ እድላቸው ያየለ፣ ስራ የማግኘት እድላቸው አነስተኛ እና ለከባድ በሽታዎች የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል። ይህ ማለት አገሪቷን ወደፊት ለማራመድ ጥቂት የፈጠራ ስራዎች፣ ጥቂት ሥራ ፈጣሪዎች፣ ጥቂት የተካኑ ሠራተኞች ይኖራሉ ማለት ነው። ለዚህም ትርፋማነት ይጓደላል ፤ የአገር ኢኮኖሚም መሆን ከሚችለው ደረጃ ሳይደርስ ከሽፎ ይቀራል።
የ2021 የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እና የዩኒሴፍ ያወጡት ሪፖርት እንደሚያሳየው፡-
በልጅነታቸው የተቀነጨሩ ህጻናት አድገው ወደ ስራ ሲሰማሩ ፤ ከእኩያቻቸው አንጻር 22% ያነሰ ገቢ ያገኛሉ።
የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ኢትዮጵያን በዓመቱ በግምት ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር (55.5 ቢሊየን ብር) የሚገመት ምርታማነት እጦት እና ለጤና አጠባበቅ ወጪ ይዳርጋል።
ኢትዮጵያ በልጅነት የሚያጋጥም የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በሚያስከትለው የረዥም ጊዜ መዘዞች ምክንያት በየዓመቱ 16.5 % የሚገመተው የሀገር ውስጥ ምርት ታጣለች።
እስቲ አስቡት ለእያንዳንዱ 6 ብር የሚገመት የኢኮኖሚ አቅም አንድ ብር በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት ይጠፋል። መቀንጨር ከግለሰብ አልፎ የሀገርን ኢኮኖሚ ይቀነጭራል ማለት ይሄ ነው።
ታዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?

መፍትሄዎቹ ሳይታለም የተፈቱ ናቸው። አዲስ አይደሉም እናቃቸዋለን። ውድም አይደሉም። ከኛ የሚፈለገው ቁርጠኝነት ነው። ለውሳኔ ማርፈድ የለብንም።
✅ በእናቶች እና ህፃናት አመጋገብ ላይ (በተለይ በመጀመሪያዎቹ 1,000 ቀናት ውስጥ) በሁሉም ባለድርሻ አካላት በደንብ መሰራት ይኖርበታል።
✅ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ፕሮግራሞችን ማገዝ እና ማጠናከር ላይ አሁንም በይበልጥ መሰራት አለበት።
✅ በተለይ እንደማህበረሰብ ሴቶችን በትምህርት እና በገቢ ማብቃት ይኖርብናል። ምክንያቱም የእናቶች እውቀት የልጆች/ የቀጣዩ ትውልድ የህይወት መስመር ነው።
✅ በየሚዲያው እና በ ማህበራዊ ድህረገጾች ከሚለቀቁት የተጓዳኝ ምግብ ማስታወቂያዎች ተቆጥበው እናቶች ለመጀመሪያ 6 ወራት የጡት ወተት ብቻ እንዲሰጡ ማስተማር ይኖርብናል። ከ6 ወራት በኋላ ለሚጨመሩ ምግቦች የተመጣጠነ ምግብ እንዲጠቀሙ መምከር ይኖርብናል።
የህጻናት አመጋገብ ላይ መስራት እጅጉን አትራፊ ነው። መቀንጨርን ለማስወገድ የማናወጣው አንድ ብር እስከ 16 ብር ይመልሳል።
ምን ያስባሉ?
ለህጻናት የተመጣጠነ ምግብ አስፈላጊነት ግንዛቤ አስጨብጠው መቀንጨርን ይግቱ።
የተቀነጨረ ልጅ የሌለበትን ኢትዮጵያን እንፍጠር!
Comments